ከክልል ቡናና ሻይ መዋቅር የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር ምክክር ተካሄደ!

ጥር 07/2013 ዓ.ም፡ አዳማ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ከፌዴራል እና ከክልል ቡናና ሻይ መዋቅር የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር በዛሬው እለት ምክክር አካሂዷል፡፡ ከተለያዩ ዞን እና ወረዳ የተወከሉ ባለሙያዎችም ተሳትፈውበታል፡፡

ክቡር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) የባለስልጣን መ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ እንዳሉት ቡና የብዙ ሚሊዮን ዜጎች መተዳደሪያ፣ የአገሪቱም የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ቢሆንም የተፈለገውን ያህል ገቢ ሊገኝበት ስላልቻለ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ተቋቋሞ የተለያዩ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያዎች ወጥተው ተግባራዊ ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ በተለይ ከባለፉት ሁለት አመታት ወዲህም ምርትና ምርታማነቱን ከማሳደግ፣ የገበያ አሰራሩን ከማዘመን እና የሚስተዋሉ ችግሮችንም ከመቅረፍ አንጻር የተለያዩ አሰራር ስርዓቶች መዘርጋታቸውን አስታውሰው በቅርቡም ሪፎርም ተካሂዶ የተለያዩ የግብይት አማራጮች መዘርጋታቸውንና የሽኝት አሰራር መመሪያም በስራ ላይ መዋሉን፣ ለመረጃ ልውውጥ የሚረዳም ሶፍትዌር ተግባራዊ መደረግ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ እነዚህ የተካሄዱ የአሰራር ስርዓቶች በተለይም ባመረተው ምርት ተጠቃሚ ሊሆን ያልቻለውን አርሶ አደር ኑሮ ለመለወጥ ታልሞ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡አቶ ሻፊ ዑመር የገበያ ልማትና ቁጥጥር ምክትል ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው በተዘጋጁ የቡና ሪፎርም እና የሽኝት አሰራሮች ዙሪያ በቅርቡ በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ ከተሞች ለሚመለከታቸው አካላት ሰፋ ያለ ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰው፤ በዛሬው እለት የተዘጋጀው መድረክ ዓላማም ግንዛቤውን ለተሳታፊው ለመግለጽ፣ ጠቃሚ ሀሳቦችን ለመለዋወጥ እና የመፍትሄ ሀሳቦችንም ለማመንጨት እንዲቻል ታስቦ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ከዚህ በመቀጠልም የቡና ሪፎርም እና የሽኝት አሰራሮች ዙሪያ በባለስልጣን መ/ቤቱ ባለሙያዎች ሁለት ሰነዶች ቀርበው ሰፋ ያለ ውይይት ተካሂዶባቸው፣ ከመድረኩ ምላሾችና ማብራሪያ ከተሰጠ በኃላ ተጠናቋል፡፡